አንዳንድ ጊዜ በተለምዶ የተቀበልናቸው፤ እኛም ሳንመረምር ዝም ብለን የምናደርጋቸው እና የምንናገራቸው ነገሮች፣ የያዙት እውነታ ከሚታወቀው በተቃራኒ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ አለ፡፡ ትምህርት የማይገባውን፣ ሰነፉን እና ደደቡን፣ ሥራ ጠሉን እና ዘረጦውን ለመግለጥ «እገሌ ድንጋይ ነው» እንላለን፡፡ የሌላውን ሀገር አላውቅም እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እንዲያ ብሎ መሳደብ እና ድንጋይን ለውጥ ለሌለው፣ ለሰነፍ እና ለሥራ ጠል አእምሮ ምሳሌ ማድረግ የምንችል አይመስለኝም፡፡
ስለ ኢትዮጵያ ፊደል አመጣጥ ሊጠየቅ የሚችለው መረጃ ድንጋይ ነው፡፡ ቀደምት ሳባውያን ታሪካቸውን እና የጉዞ ዘገባቸውን፣ ንግግራቸውን እና እምነታቸውን ጽፈው ያስቀመጡት በድንጋይ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የምንጠቀምበት እና የምንኮራበት ፊደል እንዴት እና ከየት ተገኘ ብለን ብን መረምር የመረጃው ባለቤት ድንጋይ ነው፡፡ ፊደላችንን ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩትን የጥበብ መሣርያዎቻችንን፣ የጦር መሣርያዎቻችንን፣ የእህል ዓይነቶቻችንን ፣ የምንጠቀምባቸውን ከብቶች፣ የዛፎቻችንን እና የማዕድናት ሀብቶቻችንን እንኳን የምናገኘው ከድንጋይ ላይ መረጃዎቻችን ነው፡፡
የኢትዮጵያ የጥንቱ ግዛት ከየት ተነሥቶ የት ይደርስ እንደ ነበር፣ ማን ማን የተባሉ ሕዝቦች በአኩስም መንግሥት ሥር ይተዳደሩ እንደ ነበር፣ የትኞቹ ቦታዎች በጦርነት ገብረው እንደ ነበር፣ የትኞቹ ቦታዎች ወርቅ፣ የትኞቹስ ቦታዎች አልማዝ፣ የትኞቹስ ቦታዎች ዕንቁ ይገብሩ እንደ ነበር የጥንቱን መረጃ የያዘው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ነው፡፡
ለመሆኑ የኢትዮጵያን የብዙ ሺ ዓመታት ታሪክ የድንጋይ ያህል አሟልቶ የሚያውቀው አለ? ለቅድመ ጽሑፍ ታሪካችን ምስክሩ የአኩስም እና የደቡብ ትክል ድንጋዮች ናቸው፤ ለአኩስም ዘመን ታሪካችን ምስክሩ በአኩስም አካባቢ እና ባሕር ተሻግሮ በየመን የተገኙት የድንጋይ ጽሑፎች ናቸው፡፡ በዘመኑ የተጻፈ የታሪክ መረጃ የለም ተብሎ በባለ ታሪኮች ዘንድ «የጨለማ ዘመን» እየተባለ ስሙ የጠፋው የዛግዌ ሥርወ መንግሥት ታሪካችን እንኳን ሕያው ምስክሩ የድንጋይ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፣ ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት በኋላ ለመጣው የመካከለኛው ዘመን ታሪካችንም ከጦርነት የተረፉን መረጃዎቻችን በየዋሻዎቹ የምናገኛቸው መዛግብቶቻችን ናቸው፤ የጎንደር ዘመንም አሻራዎቹ ከድንጋይ የተሠሩት ግንቦቻችን ናቸው፡፡ ሐረር ለነበረው ሥልጣኔ እና ታሪክ ሕያው ምስክራችን ከድንጋይ የተሠራው የሐረር ግንብ ነው፡፡ እናም ሦስት ሺም እንበለው ሰባት ሺ የኛን ታሪክ ከድንጋይ በተሻለ ማን ያውቀዋል፡፡
በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውን የክርስቲያን ሙስሊም ጦርነት በተመለከተ እንኳን በሁለቱም ወገን ከተጻፉት ታሪኮች ሌላ ምስክር የምናገኘው በድንጋይ ላይ ነው፡፡ የት የት ቦታዎች ጦርነቱ ተደረገ? በወቅቱ የድል በለስ እየቀናው የመጣው የኢብን ኢብራሂም አሕመድ አልጋዚ ወታደሮች እና ተከታዮች የት ቦታ ላይ ተቀበሩ? በመጨረሻም አሕመድ አልጋዚ የት ቦታ ድል ሆነ? እያልን ብንጠይቅ በወቅቱ የነበረውን ታሪክ የምናገኘው «የግራኝ» ድንጋይ በመባል ከሚታወቁት እና በወቅቱ ከተተከሉት ትክል ድንጋዮች ይመስለኛል፡፡
ሀገራችን በጦርነት ስተታመስ፤ ሕዝቦቿም ራሳቸውን እና ሀገራቸውን ሲከላከሉ የኖሩ ናቸው፡፡ አብዛኛው ታሪካችንም የጦርነት ታሪክ ነው ይባላል፡፡ በዚህም የተነሣ አያሌ ታሪካዊ መዛግብትን አጥተናል፡፡ መጻሕፍቱ፣ ሥዕላቱ፣ ደብዳቤዎቹ፣ ንዋያቱ እና የወግ ዕቃዎቹ እየተቃጠሉም፣ እየተዘረፉም፣ በአፈር እየተበሉም አልቀውብናል፡፡ የተረፉትም ቢሆኑ እድሜ ለድንጋይ በየዋሻዎቹ ተደብቀው፣ ከአፈር መበላት እና ከእሳት፣ ብሎም ከቀበኛ የተረፉልን ናቸው፡፡ እነዚህ የድንጋይ ምሶሶ እና የድንጋይ ወጋግራ ዘርግተው የተፈጠሩ የድንጋይ ዋሻዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ አሁን የምንኮራባቸውን የብራና መጻሕፍት፣ ንዋያት እና የወግ እቃዎች አጥተን ተረት ብቻ ወርሰን በቀረን ነበር፡፡
እነዚያ የድንጋይ ዋሻዎች ንብረቶቻችንን ብቻ ሳይሆን በእነዚያ የጦርነት እና የመከራ ጊዜያት እናቶቻችንን እና አባቶቻችንንም አስጠልለው አትርፈዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ተራሮች ሥር የሚገኙት እና «ዋሻ እገሌ» እየተባሉ የሚጠሩት ለቁጥር የሚታክቱት ዋሻዎቻችን፣ የባሌው ሰብስቤ ዋሻ እና የጋሞጎፋው የቦረዳ ዋሻ ለዚህ ምስክሮ ቻችን ናቸው፡፡
ቀደምቶቻችን ሰማይ ሰማዩን ብቻ ሲያዩ አልኖሩም፡፡ ምድር ንም በሚገባ ዐውቀዋት ነበር፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ የምናገኛቸውን የድንጋይ ጥበቦቻችን የተሠሩባቸው ዐለቶች ተመሳሳይ ጠባይ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚያ ጠቢባን ድንጋዮቹን በሁለት መመዘኛ ነው ሲመርጧቸው የኖሩት፡፡ ቅርጽ ለማውጣት የሚያስችል እና ረዥም ዘመን ለመኖር ዐቅም ያለው፡፡ በሁለቱም ተሳክቶላቸዋል፡፡ የሚገርመው ግን እነዚህን መመዘኛዎች የሚያሟላውን ድንጋይ ለማወቅ የሚጠይቀውን የጂኦሎጂ ዕውቀት ከየት አገኙት? የሚለው ነው፡፡
አንድ ሊቅ «ኢትዮጵያውያን ማለት ድንጋይ ሲያናግሩ የኖሩ ሕዝቦች ናቸው» በማለት የተናገረው እውነቱን መሆን አለበት፡፡ መሬቱን ፈልገው፣ ድንጋዩን አጥንተው፣ መርጠው እና አለዝበው ዘመናትን የሚሻገር የሥልጣኔ አሻራ መተው የቻሉት ድንጋይ የማናገር ችሎታ ስለነበራቸው መሆን አለበት፡፡ እነዚያን ድንጋዮች ቤት ብቻ አይደለም የሠሩባቸው፡፡ መሠዊያቸውን፣ መስቀሎቻቸውን እና ደወሎቻቸውንም ሠርተውባቸዋል፡፡ በወሎ፣ በጎንደር እና በጣና ገዳማት የምናገኛቸው የድንጋይ ደውሎች ድምፃቸው ከመዳብ እና ከብረት ደውሎች ይበልጣል፡፡ ለዚህ የተስማማውን፣ ድምፅ ሊያወጣ የሚችለውን የድንጋይ ዓይነት በምን ዐወቁት? ወይስ ያን ጊዜ የጂኦሎጂ ትምህርት ነበረ እንዴ?
ምናልባትም ቀደምቶቻችን የተፈተነ ሕይወትን የሚወድዱ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ በቀላሉ ከእንጨት፣ሣር እና ቅጠላ ቅጠል ሊሠሯቸው ይችሉ የነበሩትን ነገሮች ከባድ ከሆነው እና ልዩ ችሎታን እና ቴክኖሎጂ ከሚጠይቀው ከድንጋይ ለመሥራት የፈለጉት ተፈጥሮን ለመፈተን፣ ዕውቀትንም ለመገዳደር ይመስለኛል፡፡ የጀግንነታቸው አንዱ መገለጫም ጠላትን በመቋቋም ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮን ተፈታትነው በማስገበርም ጭምር እንዲሆን ሳያስቡ አልቀሩም፡፡ በዚህ መልኩ መከራን ተቋቁሞ ማለፍን አስቀድመው ከተፈጥሮ ጋር ባደረጉት ትግል ስለ ለመዱት ሳይሆን አይቀርም እነዚያን ክፉ ጊዜያት ታሪክ እና ቅርስን ጠብቀው ለማሳለፍ የቻሉት፡፡
ክርስቲያንም ሙስሊምም ያልነበሩት ቀደምት የዳአማት መንግሥታት ታሪካቸውን ያቆዩት በድንጋይ ነው፣ በክርስትናቸው የታወቁት የዛግዌ ነገሥታት እና ሕዝቦችም ታሪካቸውን ያቆዩት በድንጋይ ነው፡፡ ሙስሊም የተነበሩት ግዛቶቻችን እና ሕዝቦችም ታሪካቸውን ያቆዩት በድንጋይ ላይ ነው፡፡ በትግራይ፣ በላስታ እና በጎንደር ከ3000 በላይ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እናገኛለን፡፡ በአርጎባ «ራሳ» አካባቢ ደግሞ አርጎባዎች «ቱሉል» ብለው የሚጠሯቸው ወደ 3000 የሚጠጉ በባለሞያ የተቀረጹ የድንጋይ ምስሎች እናገኛለን፡፡ እናም፣ ምንም በሃይማኖት ብንለያይም ሥልጣኔያችን ግን በድንጋይ ላይ ሠፍሮ አንድነታችንን ይመሰክርብናል፡፡
ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለውን የኢትዮጵያውያንን አንድነትስ ቢሆን ከድንጋይ በተሻለ ማን ይመሰክረዋል፡፡ አንድ ሰው እንዳ ለው «እስክስታ እና ድንጋይን ያህል የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት የሚያሳይ ባሕላዊ ገጽታ የለም»፡፡ ትግራይ ላይ ከወደ አንገት እና ትከሻ የጀመረው እስክስታ፣ አገው እና አማራ ላይ ሲደርስ አንገትን ከትከሻ ያያይዝና፤ ኦሮሚያ ላይ አንገትን፣ ትከሻን እና ወገብን ከእጅ እንቅስቃሴ ጋር ያዛምዳል፡፡ ወላይታ እና ሐድያ ላይ ሲወርድ ደግሞ ወገብን ታክኮ ወደ ዳሌ ዝቅ ይላል፡፡ ከዚያም ደቡብ ጫፍ ሐመሮች ላይ ሲገባ እስክስታው በእግር ይጨርሳል፡፡ ያኔም ኢትዮጵያ አንድ ሰው ሆና ትታያለች ማለት ነው፡፡
ድንጋይም እንዲሁ ነው፡፡ ከሰሜን አኩስም እስከ ባሌ ተራሮች፣ ከምዕራብ ኦጋዴን እስከ አሶሳ፣ ኢትዮጵያ በታሪካዊ የድንጋይ ሐውልቶች የተሞላች ናት፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ እነዚህ የድንጋይ ሐውልቶች ከመቃብር እና ከታሪካዊ ሁነቶች ጋር የተያያዙ መሆናቸው ነው፡፡
የአኩስም ሐውልት በታላላቅ የአኩስም ነገሥታት መቃብር ላይ መታሰቢያ ሆኖ ቆሟል፡፡ ከአዲስ አበባ ደቡብ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ጀምሮ በሲዳማ፣ ወላይታ፣ ሐድያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ፣ በሰሜን በአዋሳ ሐይቅ፣ በምዕራብ ደግሞ በአባያ ሐይቅ ተከብቦ የሚገኘውና ከ150 በላይ ታሪካዊ ሥፍራዎችን የያዘው የድንጋይ ሐውልቶች ስብስብ፣ እንደ ሰሜኑ ሁሉ የመቃብር ሥፍራዎችን እና ታሪካዊ ሁነቶችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለይም በአርሲ እና ባሌ የምናገኛቸው ሐውልቶችም ይህንኑ የሰሜን እና ደቡብ እሴት ተጋርተው፣ አንድነታችንንም መስክረው ይሄው ዛሬም ይታያሉ፡፡
ድንጋይ ሥልጣኔያችንን ብቻ ሳይሆን ጀግንነታችንንም ሲመሰክር የኖረ ነው፡፡ መሣርያ እንደ ልብ ባልነበረበት በዚያ ዘመን ሉዓላዊነታችን ታፍሮ፣ ድንበራችን ተከብሮ፣ የኖረው በድንጋይ ጭምር ነው፡፡ ቆንጥር ለቆንጥር መወርወር፣ ተራራ ለተራራ መኖር የለመደው ሐበሻ በተራሮች ጫፍ መሽጎ ይለቅቀው በነበረው ናዳ ያለቀውን ጠላት ያህል ሌላው መሣርያችን መጨረሱን እጠራጠራለሁ፡፡ ከሜዳማ አካባቢዎች ይመጡ የነበሩት አብዛኞቹ የውጭ ጠላቶች ከመሣርያችን በላይ መቋቋም ያቃታቸው ለሀገሩ ልጅ ብቻ ይበገር የነበረውን መልክዐ ምድራችንን ነው፡፡
እናም ድንጋይ የታሪካችን፣ የፊደላችን፣ የሥልጣኔያችን፣ የእምነታችን፣ የቀጣይነታችን፣ የአንድነታችን፣ የኅብራችን መገለጫ ከሆነ «ድንጋይ» እንዴት ስድብ ይሆናል?
No comments:
Post a Comment