Tuesday, 13 March 2012

የሁለት ቤት ምክር

ከአማራ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡
የፍየል እና የነብር ግልገሎች በአንድ ሜዳ ላይ አብረው ሲጫወቱ ዋሉ፡፡ማታ ሁለቱም ወደ የቤታቸው ገቡና ለእናቶቻቸው ውሏቸውን ነገሯቸው፡፡«እማየ» አለ የነብር ግልገል፡፡ «ዛሬ ወደ ኋላ የተቆለመመ ቀንድ ካለው፡፡ከኋላው ላይ በቆዳ የተሸፈነ ሥጋ ነገር ከተንጠለጠለበት፤ ሲጮኽሚእእእእእእ ከሚል ግልገል ጋር ስጫወት ዋልኩ፡፡ እንዴት ጨዋታ ዐዋቂመሰለሽ»፡፡
እናት ከንፈሮቿን በምላሷ አራሰችና «የኔ ሞኝ እኔ እናትህ ቀኑን ሙሉስንከራተት የምውለው ምን ፈልጌ መሰለህ፤ እርሱን ፍለጋኮ ነው፡፡ ለመሆኑከማን ጋር እንደዋልክ ታውቃልሀ?» አለችው፡፡
ግልገሉ ባለማወቅ አንገቱን ነቀነቀ፡፡
«ሲበሉት ከሚጥመው፣ ሲቆረጥሙት አንጀት ከሚያርሰው ከፍየል ግልገልጋርኮ ነው»
ግልገሉ በፀፀት አንገቱን ነቀነቀ፡፡
«በል ነገ አብራችሁ የምትጫወቱ መስለህ አንገቱ ላይ በጥርስህ ትጨመድድናእየጎተትክ ታመጣዋለህ» አለችው፡፡ ተቀበለ፡፡ መሸም፡፡
በፍየልም ቤት እንዲህ ነበረ፡፡
«ዛሬ እማዬ ዝንጉርጉር መልክ ካለው፣ ቁመተ ሎግላጋ፣ ሲስቅ ድመትከሚመስል፣ ረዣዥም ጥፍር ካለው ልዩ ግልገል ጋር ስጫወት ዋልኩ»አላት፡፡ ክው አለች እናቱ፡፡ አሁን የመጣ መስሏትም በግራ በቀኟ ገልመጥገልመጥ አለች፡፡ ይሰማት ይመስል ወደ ግልገሏ ጆሮ ተጠግታ
«ከማን ጋር እንደዋልክ ታውቃለህ?» አለቺው፡፡
አንገቱን ወደ ቀኝ እና ግራ ወዘወዘ፡፡
«እርሱኮ የነብር ግልገል ነው፡፡ የነብር ግልገል የነብር ልጅ ነው፡፡ እኔ ነፍሴእስክወጣ ስሸሽ የምውለው ከርሱ አይደለም ወይ፡፡ የነብር ዓይን ወደ ፍየልየፍየል ዓይን ወደ ቅጠል የሚባለውን አልሰማህም ወይ
ግልገሉም ዕጢው ዱብ አለ፡፡ እዚያው ባለበት ቀዘቀዘ፡፡
«ታድያኮ ነገም ልንጫወት ተቀጣጥረናል» አላት፡፡
«ከነብር ጋር መጫወት ከሞት ጋር መጫወት ነው፡፡ የኛን ዘሮች አድነው የፈጇቸው የርሱ አያቶች እና ቅድመ አያች ናቸው፡፡ ስለ ነብር ስንት ተዘፍኗል፤ ስንት ተተርቷል፡፡ ስንት ተብሏል፡፡ ዛሬ ዛሬ ነው ትንሽ ተንፈስ ያልነው ልጄ፡፡ ምንም ቢሆን የትናንቱን አትርሳ፡፡ አንተ ተደብቀህ ለብቻህተጫወት፡፡ በድንገት ካየኽው ሽሽ፣ ከተከተለህም ሮጠህ አምልጥ» አለቺው፡፡
እህ በሚል ስሜት አንገቱን ወደላይ እና ታች ወዘወዘ፡፡ መሸም፡፡
በማግሥቱ የፍየሉ ግልገል ቀስ ብሎ ግራ ቀኝ እያየ ወደ መስክ ወጣ፡፡ ምንምነገር የለም፡፡ እየፈራ እየቸረ ቅጠል መቀንጠስ ጀመረ፡፡ ጥቂትእንደቀነጣጠበ ድምፅ ሰማ፡፡ ዘወር ሲል የነብሩ ግልገል ወደርሱ እየመጣነው፡፡ ፊቱን ወደ ነብሩ ግልገል አዙሮ ወደ ኋላው ማፈግፈግ ጀመረ፡፡
«የት ትሄዳለህ? እንጫወት እንጂ» አለው የነብሩ ግልገል
«አይ እናቴ ትፈልገኛለች፤» እያለ ወደ ኋላው ማፈግፈጉን ተያያዘው፡፡
«ትናንት ለዛሬ ተቀጣጥረን አልነበረም እንዴ» የነብሩ ግልገል ጠየቀ፡፡
«ተቀጣጥረን ነበር»
«ታድያ ለምን ትሸሻለህ »
«አየህ እናንተ ቤት የተመከረው ምክር እኛም ቤት ተመክሯል» አለውናፈረጠጠ፡፡
ዛሬ ዛሬ በየኮሌጆቻችን እና ዩኒቨርሲቲዎቻችን የሀገሬ ልጆች በሁለት ቤትበሚመከር ምክር ተጠምደው ይታዩኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የነብር እናየፍየል ግልገል አብረው የሚውሉባቸው ተቋማት መሆን ነበረባቸው፡፡ነብርም አዳኞቹን ፍየልም አራጆቹን ሳይፈራ፣ ፍየል በነብር ሳይጠቃ፣ነብርም በፍየል ጌቶች ሳይታደን የሚውሉበት መስክ ነበረ፡፡
ግልገሎቻችን ግን ለዚህ አልታደሉም፡፡ አማራው ለብቻው፣ ትግሬውለብቻው፣ ኦሮሞው ለብቻው፣ ሶማሌው ለብቻው፣ ወላይታው ለብቻው፣ሲዳማው ለብቻው፣ አፋሩ ለብቻው፣ ሌላውም ለብቻው ሲመክርበትየሚያድር ቤት እየሆነ ነው፡፡ መምከሩ ብቻውን ደግሞ ባልከፋ፡፡የሚመከረው ስለ ሌላው መሆኑ እንጂ፡፡ እገሌ ጠላትህ ነው፣ ጨቋኝህ ነው፣የሚንቅህ ነው፣ ከርሱ ራቅ፣ አብረህ አትዋል፣ አብረህ አትጠጣ፣ በርሱ ቋንቋአትናገር፣ እየተባለ ነው ሲመከር የሚያድረው፡፡
በሀገሪቱ የመጀመርያው ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ሲቋቋም በአሮጌው ሕንፃግድግዳ ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎ ነበረ፡፡ «ኩሎ አመክሩ ወሠናየ ግበሩሁሉን ፈትኑ መልካሙንም» ያዙ፡፡ የትምህርት ተቋማት መርሕ ይሆን ዘንድነበር የተለጠፈው፡፡ ታድያ ይህ ጥቅስ ሁሉን የሚፈትን ሳይሆን የራሱን ብቻየሚያይ፣ ሌላውንም በጥላቻ የሚቃኝ፣ ብሎም ስለ ሌላው የነብር እና ፍየልምክር በየጎሬው ሲመክር የሚያድር ተማሪ ሲያይ ምን ይል ይሆን»
የነብሩም የፍየሉም እናቶች ለግልገሎቻችው የነገሯቸው የእነርሱን ቁርሾነው፡፡ፍርሃታቸውን ነው፡፡ የነብር እና የፍየል ግልገል አብረው የመዋላቸውጥቅም አልታያቸውም፡፡ አብረው የመዋላቸው አዲስ ታሪክአልተሰማቸውም፡፡ አብረው የመዋላቸው ሀገራዊ ጠቀሜታአልተዋጠላቸውም፡፡
ምንጊዜም ትውልድ ካለፈው የተሻለ ካላሰበ፣ ያለፈውን ችግር ፈትቶ፣ የተሻለዓለም ካላሳየ ትውልድነቱ ምኑ ላይ ነው? ግልገሎቹ ለየብቻ፣ ያም በጉሮኖውይኼም በዋሻው የተመከረውን ብቻ የሚያስፈጽሙ ከሆነ እነዚህ አሮጌግልገሎች እንጂ አዲስ ትውልዶች እንዴት ይሆናሉ፡፡
ለመሆኑ ስለ ኦሮሞ ጉዳይ ኦሮሞዎች ብቻ መነጋገር፣ መምከር፣ መጨነቅአለባቸው? የኦሮሞ ጉዳይ የአማራ፣ የትግሬ፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣ የወላይታጉዳይ አይደለም ያለው ማን? ማነው ይህንን አጥር የሠራው? የትግሬን ጉዳይማነው የትግሬ ብቻ ነው ያለው? ሌላው አያገባውም? አያስጨንቀውም?አይመለከተውም? ለምንድን ነው በየጉሮኗችን እና በየዋሻችን ብቻችንንየምንመክረው፡፡ የኦሮሞ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም እንዴ? የአማራጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም እንዴ፣ የሲዳማ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይአይደለም እንዴ፣ የሶማሌ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም እንዴ?ለምንድን ነው ጠብበን እና አጥብበን የመንደር ጉዳይ የምናደርገው፡፡ ጎበዝእዚያም ቤት እንደ ሚመከረውኮ እዚህም ቤት ይመከራል፡፡ እነ እንቶኔእንደሚያስቡትኮ እና እንትናም ያስባሉ፡፡
ለምን አብረን አንመክርም? የነብርም ሆነ የፍየል ግልገል ጠላትነቱየሚቀጥልበትን መንገድ ብቻ ነው በየበኣታቸው ሆነው የመከሩት፡፡ እኛምኮከእነርሱ አልተሻልንም፡፡ ለየብቻ ተሰብስበን ከተቻለ ስለ ነባሩ ጠላታችንእንመክራለን፤ ካጣንም ጠላት እንፈጥራለን፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በየበኣቱ ብቻ የሚመከርባቸውና የበኣት ጠላትየሚፈራባቸው ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ ዘር እና እምነት፡፡ በክርስቲያኑም ዘንድነብር እና ፍየል አለ፡፡ በሙስሊሙም ዘንድ ነብር እና ፍየል አለ፡፡ እነዚያንምለብቻ ጠርተው በቤታቸው የሚመክሯቸው አሉ፡፡ እነዚህንም ለብቻጠርተው በቤታቸው የሚመክሯቸው አሉ፡፡ የነብር እና የፍየል የማያውቁትንጠላትነት የገዛ ወላጆቻቸው እንደተከሉባቸው ሁሉ እነዚህንም «እገሌ ጠላትህነው ተጠንቀቀው» እያሉ ጠላት ተክለው ጠላት የሚያበቅሉ ሞልተዋል፡፡
መጀመርያ ክርስቲያኑ እና ሙስሊሙ ለየብቻ እንዲመክሩ አድርገውየጠላትነትን መንፈስ ዘሩ፡፡ ቀጠሉና በሙስሊሙ መካከል ነብር እና ፍየልፈጠሩ፤ በክርስቲያኑ መካከልም ነብር እና ፍየል አፈሩ፡፡ ግን እስከ መቼከነብር ተጠንቀቅ፣ ፍየልን እነቅ እየተባልን እንኖራለን? አሁን በሁላችንምልብ ውስጥ የተጠቂነት ሥነ ልቡና እየሠረፀ ነው፡፡ ሁሉም ተበድያለሁ፣ተገፍቻለሁ፣ ተጠቅ ቻለሁ፣ ተጨቁኛለሁ፣ ተደፍሬያለሁ፣ ተዋርጃለሁ እያለብቻ ነው የሚያስበው፡፡
በአንድ ወቅት ከወንዝ ወዲህ እና ወዲያ የሚኖሩ መንደርተኞች ነበሩ አሉ፡፡ታድያ የሁለቱ መንደርተኞች ልጆች ወንዙ ሲገናኙ ያዩ ወላጆቻቸውእየጠሩ «እነዚያ መንደርተኞች ቡዶች ናቸውና አትቅረቧቸው» እያሉልጆቻቸውን ይመክሩ ጀመር፡፡ የዚህኛውም መንደር ሆነ የዚያኛው መንደርምክር ተመሳሳይ ነበረ፡፡ እነዚህም እነኛን እነኛም እነዚህን ቡዶች ናቸውብለው ፈርተው በየመንደራቸው ቀሩ፡፡
ይህንን ያዩ የሁለቱ መንደር ሽማግሌዎች አንድ ቀን ተነጋገሩና ወንዙ ዳርተገናኙ፡፡ እናም እንዲህ ብለው ጠየቁ «ለመሆኑ ቡዳው ማነው) ያን ጊዜአንዲት እናት ተነሡና «እነርሱም እኛን ይላሉ እኛም እነርሱን እንላለን½ቡዳው አልታወቀም ግን እንበላላለን» አሉ አሉ፡፡
የየእምነቱ ሰዎች ችግሩን ከሌላ ቦታ እየፈለጉት እነዚያኞቹን ቡዶችእያልናቸው ነው እንጂ ችግሩ ያለው ከራሳችን ነው፡፡ ኢትዮጰያ ውስጥአማኞቹን የሚመጥን የእምነት ተቋም እና የእምነት አባት እጥረትተከስቷል፡፡ በእስልምናም እንሂድ በክርስትና አማኞች በእምነትአመራሮቻቸው እና አባቶቻቸው፣ ተቋሞቻቸው እና አሠራሮቻቸው ሊረኩአልቻሉም፡፡
አሁን በአማኞች መካከል በየጉሮኗችን እንድንመክር እና ቡዶቹ እነዚያኞቹናቸው እንድንል ያደረገን ተቋማዊ ችግሮቻችንን መፍታት ባለመቻላችንነው፡፡ የአስተዳደር በደል፣ ሙስና፣ ዝርፊያ፣ ለሥልጣን መሯሯጥ፣ የእምነትሕግጋትን ለጥቅም ሲሉ መሸጥ፣ እግርን ቤተ እምነት አድርጎ ራስን ፖለቲካላይ መንተራስ፣ የዘመድ አዝማድ አሠራር፣ ለታሪክ፣ ባህል እና ቅርስ ግዴለሽመሆን የኢትዮጵያ ቤተ እምነት ተቋማት የጋራ ጠባያት እየሆኑ ነው፡፡
እነዚህ አካላት እኛ ተስማምተን ወደ እነርሱ እንድናይ ስለማይፈልጉበየጉሮኗችን ለየብቻ ይመክሩናል፡፡ እኛም የማናውቀውን ጠላት እናውቃለን፣መንገዳችንም እምነት ተኮር መሆኑ ቀርቶ ጠላት ተኮር ይሆናል፡፡ ይመስለናልእንጂ አንደኛችን አዝነን ሌላችን ልንደሰት አንችልም፡፡ አንዳችን አንገታችንደፍተን ሌላችን ቀና ልናደርግ አንችልም፡፡ ነፍስ ኄር አባ እንየው ውቤ ዘአሶሳበደርግ ጊዜ ከዞኑ ኢሠፓ /ቤት ለሠፋሪ ሙስሊሞች የመስጊድ መሥሪያቦታ ሊያስፈቅዱ ሲገቡ የኢሠፓ ጸሐፊው «እርስዎ ክርስቲያን ሆነው ስለሙስሊሙ የሚከራከሩት ለምንድን ነው ብሎ ሲጠይቃቸው «ወዳጄሙስሊሙ እያዘነ ክርስቲያኑ ሊደሰት አይችልም፣ እምነት የግል፣ ደስታ ግንየጋራ ነው» ነበር ያሉት፡፡
ይልቅስ ጎበዝ ሞኞች አንሁን፡፡ በጋራ እንምከርና ጠላትነቱን ትተን ፊታችንንየየራሳችንን ቤት በጋራ ወደማስተካከል እንምጣ፣ ተቋማዊ አሠራሮቻችንንእንፈትሻቸው፡፡ ለምንድን ነው በእምነት ተቋሞቻችን እና በእምነትመሪዎቻችን እኛ ኢትዮጵያውያን ልንረካ ያልቻልነው? ለዚህ ጥያቄ የጋራምላሽ እንፈልግ፡፡
ያን ጊዜ ነብር እና ፍየል አብረው ይውላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment