
ሕይወት በባዕድ ምድር (፪ጴጥ. ፪፥፰)
የርዕሳችን መነሻ የሆነው በ፪ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ ፪ ላይ የምናገኘው ታሪክ ነው። “ጻድቅ ሎጥም እያየና እየሰማ፣ አብሮአቸውም እየኖረ በክፉ ሥራቸው ዕለት ዕለት ጻድቅት ነፍሱን ያስጨንቃት ነበር።” ፪ጴጥ. ፪፥፰
ሎጥ ኃጢአትን የዕለት ከዕለት ተግባራቸው ካደረጉ ሰዎች ጋር ለመኖር የተገደደው በዘፍ ፲፫ ላይ እንደምናነበው ከአጎቱ ከአብርሃም ጋር ይኖርበት የነበረው ቦታ ስለጠበባቸው በእረኞቻቸው መካከልም እየተፈጠረ የነበረው ጥላቻ ወደ እነርሱ እንዳይጋባ ራቅ ወዳለ ቦታ መሄድ ስለነበረበት ነበር። ለመለያየት ሲወስኑም ለሎጥ እንዲመርጥ ዕድል በተሰጠው ጊዜ የመረጣት ውሃ የሞላባትን ለምለሟን ሰዶምን ነበር። ሎጥ ግን በጎረቤቶቹ መካከል እየኖረ ዕለት ዕለት የሚሠሩትን ሥራ እያየና እየሰማ ይጨነቅ ነበር። ጎረቤቶቹ ግን ማንኛውንም ኃጢአት ከመስራት ወደ ኋላ የማይሉ ነበሩ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከው የመጡ መላእክትን እንኳን ሳይቀር በግብር ለማወቅ ከሎጥ ጋር ግብግብ ሲገጥሙ በዘፍ ፲፱:፬-፲፩ ላይ እናነባለን።
በተለያየ ምክንያት ከሀገራችን ወጥተን በስደት ሕይወትን ለመግፋት ግድ የሆነብን ሰዎች ዛሬ ከአባታችን ከሎጥ የምንማረው ብዙ ነገር አለ። ፈተና የክብር ማግኛ መንገድ ነዉ። ስለሆነም ደጋግ አባቶቻችን ፈተና ሲርቅላቸዉ አይወዱም ነበር፤ ከቅዱስ እግዚአብሔር ጋር ለመሆናቸዉ አንዱ ማረጋገጫቸው በፈተና መጎሸማቸዉ ስለሆነ። ጻድቅ ሎጥ አስጸያፊ የሆነ ግብረ ሰዶም በሚፈጸምባት ከተማ እየኖረ ከእግዚአብሔር አልተለየም ነበር፤ ነፍሱን በብዙ ያስጨንቃት ነበር እንጂ። አበ ብዙሃን የተባለ አብርሃም ስለነዚያ ሰዎች ድኅነት ልመና ቢያቀርብም በከተማዋ 10 ደጋግ ሰዎች ባለመገኘታቸዉ ቅዱስ እግዚአብሔር ከተማዋን ሊያጠፋት በወሰነ ጊዜ ከነዚያ ሰዎች ኃጢአት ተሳታፊ ያልነበረ ጻድቅ ሎጥ እና ቤተ ሰዎቹን ለማውጣት መላእክት ተልከዋል።
ጻድቅ ሎጥ በመጀመሪያ የአካባቢዉን ልምላሜ እና ለከብቶቹ ምቹ መሆኑን እንጂ የነዋሪዎቹን ክፋት አልመረመረም። በመሆኑም የነዚያን ሰዎች ገደብ የለሽ የኃጢአት ሕይወት በማየትና በመስማት እየተጨነቀ መኖር ግድ ሆነበት። ለእግዚአብሔር ሰዉ የሰዶም ሰዎች ሕይወት የተጠላ ነዉና። በየአዝማናቱ በክፉ መንገድ የሚጓዘው ሰዉ በቁጥር አያሌ ነው። ቅዱሳን ሰዎች የቅድስና እና የብጽእና ክብር የተቀዳጁት ከነዚህ ሰዎች ጋር እየኖሩ በክፉ ሥራቸው ሳይተባበሩ ራሳቸውን ጠብቀዉ በመኖራቸዉና ፈተናዉን በማሸነፋቸው ነዉ። ሁሉ በደለኛ ነዉ እኔ እንዴት ብቻየን መኖር ይቻለኛል? የሚል አዕምሮ የለባቸዉም። እንዲህስ ቢሆን ጽድቃቸዉ ግዘፍ ነስቶ ባልተናገረ ነበር።
ኖኅ በጽድቁ ዓለምን ኮነነ የተባለዉ ሰብአ ትካት (የጥንት ሰዎች) ሲበድሉ በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንቶ በመገኘቱ ነዉ። ለሎጥስ የግብረ ሰዶምን አስከፊነት ማን ነገረዉ፣ በዚያን ጊዜ የጽሑፍ ሕግ አልነበረምና። ዛሬ ግብረ ሰዶም በዓለም ተንሰራፍቶ እንዲያዉም በመንግሥታት ሳይቀር ሕግ እየወጣለት ነዉ፤ ወንድ ከወንድ፣ ሴትም ከሴት መጋባት ተጀምሯል። እጅግ የሚገርመዉ በእንስሳቱም እኮ ይሕ ይፈጸማል በማለት የሚናገሩ መኖራቸዉ ነዉ። ዓለም በቴክኖሎጂ፣ በዕዉቀት፣ በስልጣኔ እና በመሳሰሉት መጥቆ ሄዷል እየተባለ እንደገና ሰዉ ራሱን አዋርዶ ከእንስሳት ለመማር መዳዳቱ የጊዜዉን አስከፊነት ፍንትዉ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ። ቆነጃጅቱ ራቁታቸዉን ሲሄዱ፣ በየመንገዱ እንደዉሻ ሲላላሱ፣ ዝሙቱንም ያለ ሃፍረት ሲፈጽሙ እነሆ እናያቸዋለን። በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ራቁታቸዉን ሆነዉ የሚታዩበት ቦታ የተከለለላቸዉ መሆኑ ይነገራል። ወንድ ከወንድ ጋር ጋብቻ እንዳይከለከል በፍርድ ቤት ቀርበዉ ሲከራከሩ ከተፈጥሮ ሕግ ወጣን ብለዉ ቅንጣት ታክል እንኳን አይደነግጡም። ታዲያ ከሎጥ ዘመን፣ ከሰብአ ትካት የተሻሉት በምን ይሆን? ሰዉ እንስሳትን መምሰል ብቻ አይደለም ከእንስሳትም አንሷል። እንሰሳት እና አራዊት እንኳ የየራሳቸዉን ግብር ይዘዉ ይኖራሉ፤ ሰይጣንም እንኳ ስለሚበላዉና ስለሚጠጣዉ ተጨንቆ አያዉቅም። ለዚህም ነዉ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ አንተ ማስተዋል ከሌላቸዉ ዲዳ አራዊት እንስሳት ከሰይጣንም የምታንስ ስለሆነ ምን ብዬ ልጥራህ? እያለ ለመናግር የደረሰዉ።
እንግዲህ እንዲህ አይንቱ አስከፊ ኃጢአት እየተሠራና እየተነገረ ባለበት ጽንፈ ዓለም እየኖርን ነዉ። ለመሆኑ እንደ ጻድቁ ሎጥ ነፍሳችን ተጨንቃ ይሆን ወይስ እንዲያዉ “ሳይበዛ” ማየቱንም መስማቱንም እየወደድነው ይሆን? ግዙፍ መርከብን ለማስጠም ትንሽ ትበቃለች። ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረም “ነገር ሁሉ ያደክማል፤ ሰዉም ይናገረው ዘንድ አይችልም፣ ዓይን በማየት አይጠግብም፣ ጆሮም በመስማት አይሞላም”። መክ ፩፥፰.። እያንዳንዷ ዕለት የጽድቅን ሥራ እንሠራባት ዘንድ እንዲሁ ከፈጣሪያችን የተቸረችን በረከት መሆኗን አዉቅን በመስማት፣ በማየት፣ በመናገር፣ በመዳሰስ፣ በማሽተት እና በግብር ከመፈጸም ከሚገጥመን ነገር ራሳችንን እየጠበቅን እና ለጽድቅ ተጋድሎ ሰዉነታችንን እያስለመድን ነዉን? ወይስ ምን አለበት፣ የጽድቁ ሥራ ይደርሳል፣ ለብቻ መኖር አይቻል? ማሕበራዊ ኑሮ ስለሆነ ምን እናድርግ፣ አለቃየ እኮ ነዉ እና የመሳስሉትን እያልን ነዉ? ልናስተዉል የሚገባን ነገር ቢኖር የትም ሆነ የት ፈተና የማይቀር መሆኑን ነዉ። ፈተናም በተለያየ ደረጃና ሁናቴ ይመጣል እንጂ አንድ ዓይነት አይደለም።
በመጀመሪያ ከራሳችን የሚመጣ ፈተና አለ። ንዝህላልና ግድየለሽ ሆነን ማድረግ የሚገባንን ጥንቃቄ ምን አለበት ብለን ስንተዉ ፈተና ይገጥመናል። "ጥቃቅኑን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን" መኃል. ፪፡፲፭። የተባለዉ ለዚህ ነዉ ከሥጋ ፈቃድ ፈተና ይመጣል፤ መጾማችን ቅሉ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስግዛት ነዉ እንጂ ሌላ አይደለም። በነፍስና በሥጋ ፈቃዳት መካከል ሁል ጊዜ መጠላላት አለ፤ አንዱ ሌላዉን ማርኮ የራሱ ግብር ተባባሪ ለማድረግ ሁልጊዜ ይቀዋወማሉ(ገላ. ፭፣፲፯-ፍጻ)። የሥጋችንን ፈቃድ ስንፈጽም ፈቃዳተ ነፍስን መፈጸም ይሳነናል። ለዚህም ነዉ የተመሰገነ ሐዋርያ ጳዉሎስ “...የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን...” ኤፌ. ፪፣ ፫ በማለት ከማይገባ ምኞት እንጠበቅ ዘንድ የመከረን።
ሁለተኛ ከሰይጣን የሚመጣብን ፈተና አለ። እርሱ ሁል ጊዜ ተቃዋሚያችን ነው፤ የጽድቅ ጠላቷ የሐሰት አባቷ ነዉ። ስለሆነም ሓጢአት ለማሠራት ይገፋፋናል። በአገልግሎት የተጋን እንደሆነም በትዕቢት ያጠምደናል፣ በጽድቅ ሥራም እንኳ ሳይቀር አለሁበት ይላል። እርሱ ቅሉ ከማስጎምጀት፣ ከማቻኮል፣ አድርጉት አድርጉት የሚል ሃሳብ ከማቅረብ አልፎ አያስገድድም፤ ሲፈትንም ቅሉ ፈቃድ ሳይቀበል አንዳች ማድረግ አይችልም። ስለዚህ የሚጥለን በክፉ መንገዱ ለመሄድ ፈቃደኛ ሆነን ሲያገኘን ነዉ። እርሱ መቸም መች አይተኛም። ቅ/ጴጥሮስ “በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚዉጠዉን ፈልጎ እንደሚያግሣ አንበሳ ይዞራልና፤” ፩ጴጥ. ፭: ፰ና፱። በምንድን ነዉ የምንቃወመዉ? በትህትና፣ በፍቅር ጸንቶ በመመላለስ፤ ጻዲቅ ሎጥን መስሎ በመገኘት ነዋ! የኃጢአት ነቋ ሰይጣን ነዉና ኃጢአትን እንደሎጥ መቃወምና ነፍስን ለጽድቅ ማስጨነቅ ሰይጣንን መቃወም ነዉና።
በመጨረሻም ከምንኖርበት ሀገር ባሕል፣ ልምድ፣ ወግ፣ ከጓደኛ (የትምህርት ቤት፣ የሥራ...) ሊመጣ ይችላል። ቅ/ጳዉሎስ “አትሳቱ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።” ፩ቆሮ.፲፭፣፴፫ እንዳለ በማይመች አኳኋን መኖር ከጀመርን መውደቅ ይከተላል። የእናታችን ሔዋን እና የእባብ አይነት ግንኙነት (ዘፍ.፫)፣ የዲናና የሴኬም ግንኙነት (ዘፍ.፴፬)፣ የሶምሶምና የደሊላ አይነት ግንኙነት (መ.መሳ. ፲፬) መጨረሻዉ ዉርደት ይሆናል። ጻዲቅ ሎጥን ለመጨነቅ ያደረሰው የሰዶም ሰዎች የሚሠሩትን ክፉ ግብር ማየቱ ነበር። እኛንም በዋናነት ሊያስጨንቀን የሚገባዉ ይህ ነው። ማየት ወደ ምኞት፣ ምኞትም ኃጢአትን ጸንሶ ወደ መወለድ (በግብር ወደ መፈጸም) ሳያደርስ አይቀርም። የማይገባ እይታ ለከፋ ነገር ማድረሱ አይቀርምና አየሁ እንጂ ምን አደረግሁ አይባልም። አምኖን በወንድሙ ለመገደል ያበቃዉ (፪ሳሙ. ፲፫) በማይገባ እይታ እና ምኞት ተነድቶ እህቱን ትዕማርን ከክብር በማሳነሱ ነዉ። ሔዋን ከ ዕፀ በለስ የበላችዉ በዓይኗ ተመልክታ ከጎመጀች በኋላ ነዉ። አምኖንም ሔዋንም ባልንጀሮቻቸው ያዩትን እንዲፈጽሙ የሚያተጓቸዉ እንጂ ኧረ አይግባም የሚሏቸዉ አልነበሩም፤ ሔዋን አዳምን፣ አሞንም ዳዊትን ቢያማክሩ ኖሮ ያ ሁሉ ዉድቀትና ሞት ባልመጣባቸዉ ነበር።
ምን አልባት በምንኖርበት አካባቢ ባሉ ስዎች ዘንድ ጸያፍ ነገር ማየት እንደ ድንቅ ላይታይ ይችላል፣ ምክንያቱም እነርሱም በዚያ ሕይወት ዉስጥ ነዋሪዎች ስለሆኑ ክፋቱ አይታያቸዉምና። ጻድቅ ሎጥ በእነርሱ ክፉ ሥራ ነፍሱን ሲያስጨንቅ የሰዶም ሰዎች፤ ኖኅም ከጥፋት ዉሃ ለማምለጥ በእግዚአብሔር ትእዛዝ መርከብ ሲያዘጋጅ ሰብአ ትካት እንደ ሞኝ ይቆጥሯቸው ይስቁባቸዉም እንደነበር ነዉ። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን ሰዉነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰዉነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። ” ማቴ.፮፣፳፪ ማለቱ ለዚህ ነዉ።
እንግዲህ ፈተና ባንድም በሌላም መንገድ መምጣቱ የማይቀር ከሆነ ራሳችንን ጠብቀን ለመኖር እና እናንተ ያባቴ ቡሩካን ኑ (ማቴ. ፳፭፣፴፬) ብሎ ከሚያከብራቸው ቅዱሳን ጋር ለመደመር ምን እናድርግ? ከረጅሙ ባጭሩ ወስደን ከብዙ በከፊሉ ጨልፈን እንደሚከተለው ለማየት እንሞክር፦
፩ በሕገ እግዚአብሔር መኖር፦ የሰው ልጅ ከእግዚአአብሔር የተቀበለውን ሁሉ ዋጋ መክፈል የሚችለው ትዕዛዛቱን በመፈጸምና ምስጋናን በማቅረብ ብቻ ነው። አምልኮተ እግዚአብሔርን በትክክል ለመፈጸም ሕገ እግዚአብሔርን መማር ይኖርብናል። በፍፁም ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር “ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ” በማለት ነግሮናልና። የእግዚአብሔር ለመሆናችን መታወቂያዉ በትእዛዙ መኖር ነው፤ ሕግጋቱንና ትእዛዛቱን በመጠበቃችን የእርሱ መሆናችን ይታወቃል። በየትኛውም ሀገር ብንሰደድ በማንኛውም ጊዜና ቦታ የማይለወጠው እግዚአብሔር አብሮን እንዳለ መርሳት የለብንም። በሀገራችን ስንሆን ሕጉን የምንጠብቅ ከሀገራችን ውጭ በማይመች ሁኔታ ስንሆን ከሕገ እግዚአብሔር ውጭ እንድንሆን አልተፈቀደልንም። የክርስቲያን መልኩ አንድ ነው፣ በየተግኛዉም አጽናፈ ዓለም ቢኖር አካሄዱ ይገልጠዋል። ሁልጊዜም ሕይወቱ በቃለ እግዚአብሔር የተቃኘ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ስለሆነ ባነጋገሩ፣ ባኗኗሩ ይታወቃል። “ቃሉን ስበክ በጊዜዉም አለጊዜዉም ጽና”፪ጢሞ.፬፣፪ ፤ “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር” ፪ጢሞ. ፫፣፲፬፤ “ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፣ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይግኝ፣ የወይራ ሥራ ቢጎድል፣ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፣ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፣ ላሞችም በጋጡ ዉስጥ ባይገኙ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይልኛል።” ዕንባ. ፫፣፲፯ና ፲፰። ይልቁንም ዕለት ዕለት ሕጉንና ትዕዛዙን በመጠበቅ መኖር ይገባናል። አባቶቻችን አካሄዳቸውን ሁሉ በሕገ እግዚአብሔር መሰረት ማድረጋቸውን ነብዩ ዳዊት “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው”። መዝ ፻፲፰፣፻፭ በማለት ያስተምረናል።
፪. ሥጋዊ ምኞትን አለመከተል/አለማስቀደም እና ምሳሌ መሆን፦ ከፍ ብሎ ለመግልጽ እንደተሞከረዉ ፈቃደ ሥጋን መከተል ነፍስ ፈቃዳቷን እንዳትፈጽም ያደርጋታል። በመንፈስ ጀምረዉ በሥጋ የሚጨርሱ ሰዎች ትንሽ የሚባሉ አይደሉም፤ እኔ አገልጋይ ነበርኩ፣ አስቀዳሽ ነበርኩ፣ ጿሚ፣ ለሕገ እግዚአብሔር ቀናዒ ነበርኩ የሚሉ አሁን ግን በዓለም አምሮት ተዉጠዉ ያሉ ብዙ ናቸው። የአስቆሮቱ ይሁዳ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበር፤ ዴማስ የቅዱስ ጳዉሎስ ደቀ መዝሙር ነበር። ሆኖም ግን ይሁዳ በሠላሳ ብር ጌታዉን አሳልፎ በመስጠት፣ ዴማስም በተሰሎንቄ ከተማ ተማርኮ ከቅዱስ ወንጌል አግልግሎት ተለይተው ተጎዱ። የሁለቱም ከተቀደሰዉ ሕይወት መራቅ ምክንያቱ በፍቅረ ዓለም መሳብና ሥጋዊ ምኞትን ማስቀደማቸዉ ነዉ። ስለዚህ ፈቃደ ሥጋን በመግታት በጀመርነዉ የጽድቅ መንገድ መጓዝ ይገባናል። በሰብአ ትካት መካከል ኖኅ ና ቤተ ሰዎቹ፣ በሰዶም መካከልም ሎጥና ቤተ ሰዎቹ ነበሩ፣ ግን ከጽድቅ መንገድ አልወጡም። ክርስትናን በዓለም ያስፋፉት ክብር ምስጋና ይግባዉና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋለበት እየዋሉ ባደረበት እያደሩ የተማሩ 120 ቤተ ሰዎች ናቸዉ። በዙሪያቸው የነበረው ሕዝብ ሁሉ እነርሱንና አምላካቸው ኢየሱስ ክርስቶስን የሚጠላ የሚገድላቸውም ነበረ። እነርሱ ግን ከሥጋዊ ምኞት በመራቅ ሁልጊዜ ምሳሌ በመሆን ክርስትናን በዓለም ሁሉ ሰበኩ፤ ጠላቶቻቸውንም ሳይቀር የእግዚአብሔርን ልጅነት ያገኙ ዘንድ አጠመቋቸው። ስለዚህም ከአባቶቻችን የምንማረው ምንጊዜም በተማርነውና በተረዳነው ሕግና ሥርዓት መሠረት መኖር እንደሚገባን ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ በመልዕክቱ እንዲህ ሲል ጽፎልናል፤ “የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ ነፍስን ከሚዋጋ ከሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች፣ ደካሞችም እንደመሆናችሁ እለምናችኋለሁ።”፩ጴጥ ፪፥፲፩ “ክፉ ከምትሰሩ ይልቅ መልካም ሥራ እየሰራችሁ፣ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ እየተከተላችሁ መከራ ብትቀበሉ ያሻላልና።” ብሏል። ፩ጴጥ ፫፥፲፯
፫. ትዕግሥት፦ ከሥጋዊ ምኞት ለመራቅ በምናደርገው ጥረት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች መኖራቸው አይቀሬ ነው። እንዲያውም አንዳንዴ ሕግህን ስላከበርኩ ይህን ያህል መከራ ሊጸናብኝ አይገባም ብለው የሚመጻደቁ ሰዎችም አይጠፉም። ከሓጢአት ጋር ተላምደዉ፣ ካለማመን እና ከክሕደት ጋር ተዛምደዉ፣ ከክፉ ልማድና ከክፋት መንገድ ጋር ተጣብቀዉ በአመጽ እየኖሩ የጎደለባቸዉ ነገር የለም፣ እኔ ግን የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ለማግኘት ከሀገር ወጥቼ በባዕድ ሀገር መኖርና መንገላታት አገኘኝ የሚል ሃሳብ ሊመጣብን ይችላል። እንዲሁም ለሥጋዊ ሕይወት የሚያስፈልገዉን ሁሉ ለማግኘት አግባብ ባልሆነ መንገድ መሄድና ብኩን ሕይወት መምራትን እንደ መልካም ቆጥረን እንድንገፋበት የሚያበረታቱን ነገሮች በዙሪያችን ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እንዲህ አይነት አሳብ ሲመጣብን መጠራት እኮ ለማመን ብቻ አይደለም ልንል ይገባል። የቅዱስ እግዚአብሔር የሆኑት ቀደምት አበዉ እና እማት እጅግ የከፋ መከራ ተቀብለዋል፣ ስለ ርትእት እምነት ደማቸዉን አፍሰዋል፣ አንገታቸውን ለሰይፍ ጀርባቸውን ለግርፋት ሰጥተዋል። ይህ አሁን የምንኖርበት ዓለም ወደ ቀደመ አለመኖሩ የሚመለስበት ጊዜ ይመጣል። ስለዚህ ያለንበትን ሁናቴ እና የሚደርስብንን መከራ በኋላ ከሚጠብቀን ሕይወት አንጻር ስናየዉ እጅግ ያነሰ መሆኑን መገንዘብ ይግባናል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ማንም ያልተቀበለዉን ስቃይ ተቀብሏል። ወርቅንና ብርን፣ ሹመትንና መንግሥትን፣ የሰብአ ነገሥት ሽልማትንና የዚህ ዓለም ክብር በነፋስ ተገፍቶ እንደሚጠፋ ደመና ቆጠረዉ፡፤ ለሰባት ዓመት ጽኑዕ ተጋድሎዉም ሰባት አክሊላትን ተቀበለ። መከራዉ ከተቀበለዉ ክብር ጋር ሲነጻጸር ከቁጥር አይገባም። ትዕግሥት ሊኖረን ይገባል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ትዕግሥትን የመልካምነት ዘዉድ ይላታል። ቅዱስ ያዕቆብም “ እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፣ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። ... ልባችሁንም አጽኑ ጌታ መምጫዉ ቀርቦአልና።” ሲል ይመክረናል። ያዕ.፭፣፯-፲፩። አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "እስከ መጨረሻዉ የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል ማቴ. ፳፬፣፲፫ ብሎ በማይታበል ቃሉ ነግሮናል። የሚገጥመንን ፈተና በትዕሥት ስንወጣ ያኔ ክብር ይጠብቀናል። ጻድቅ ኢዮብ ፈተናዉን በመታገሡ ለትዕግሥት አብነት ሆኗል። ስሙም ተለዉጦ ኢዮባብ ተብሏል። ቅዱስ ጳዉሎስ በዕብራዉያን መልዕክቱ ምዕራፍ 11 የዘረዘራቸው ቅዱሳን ሁሉም የሚገጥማቸዉን ፈተና በትዕግሥት ተቀብለዉ ጽኑዕ ተጋድሎን ተጋድለው ፈጽመው በማሸነፋቸው ነዉ። መከራ ያለብን መሆኑንም ራሱ አምላካችን “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ዮሐ. ፲፮፣፴፫ ብሎ ነግሮናል።
፬. ማንነትን ማስታወስና የተጠሩበትን ማወቅ፦ በስደት ስንኖር የራሳችን እምነት፣ አምልኮ፣ ባሕልና ትውፊት እንደሌለን ሁሉ የባይታዋርነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርጉ ሁኔታዎች እጅግ ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜም የማንነታችን መገለጫ የሆኑትን ነገሮች ሰዎች ሲያፌዙባቸውና ሲሳለቁባቸው ተስፋ የሚያስቆርጥ የሚመስል ሁኔታ ሊገጥመን ይችላል። በዚህ ጊዜ ግን ማንነታችንን ማስታወስ ይገባናል። የትም ብንሄድ የአምልኮት መልካችን ሊቀየር አይገባውም። ይህንንም ነብዩ ኤርምያስ “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?” በማለት የአምልኮት መልካችን መቼምና የትም መቀየር የማይችል መሆኑን ያስገነዝበናል። ኤር. ፲፫፣፳፫:: እስራኤላውያንን ማርከው የወሰዷቸው አሕዛብ የጽዮንን ዝማሬ እስኪ ዘምሩልን ብለው በጠየቋቸው ጊዜ በገናዎቻቸውን ዛፍ ላይ በመስቀል ያ የጽዮን ዝማሬ በኢየሩሳሌም ምን ዓይነት ክብር ያለው እንደ ነበር በማስታወስ አንዘምርም አሉ። ልበ አምላክ ዳዊትም ማንነቱን ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር “ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ። ባላስብሽ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ” በማለት ቃልኪዳኑን ሲያከብር እንማራለን። መዝ. ፻፴፮፣፭:: ፈሪሃ እግዚአብሔር አጥር፣ ሃልዎተ ፈጣሪ ከለላ፣ ሕገ እግዚአብሔር ብርሃን ሊሆነን ይገባል። ዮሴፍን ማሰብ፣ ሠለስቱ ደቂቅንም ማስታወስ ይገባል። ዮሴፍ በባርነት፣ ሠለስቱ ደቂቅም በምርኮ እያሉ በፊታቸው እግዚአብሔርን አድርገው ከባእድ ሰዎች ጋር መተባበር፣ አማልክቶቻቸውንም መከተልን እምቢ አሉ። ሃይማኖት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፤ ለመኖር ሲባል የሚል ቋንቋ በሃይማኖት ቦታ የለዉም። ተዋሕዶተ ቃልን (ሥጋዌዉን) የማያምን ርጉም ነው፣ የአርዮስ ዉላጅ ስለሆነ ከእርሱ ፈጥኖ መለየት ይገባል። በግ በግን እንጂ ፍየልን ወይም ተኩላን መሆን አይቻላትም፣ ጠባዩአ እና ግብሯ ከነሳቸዉ የተለየ ስለሆነ። ከዚሁም ጋር ለምን ከሀገር እንደወጣንም ማሰብ ተገቢ ነዉ። ከሀገር መዉጣታችንን ከዱባ ተክል ጋር ማነጻጸር እንችላለን። የዱባ ፍሬ ከበቀለች በኋላ እየተሳበች ትሄዳለች። ዱባ ፍሬ ለማፍራት የምትሄድ ከሆነ የእኛም ከሀገር መዉጣታችን እንዲሁ ፍሬ ለማፍራት ነዉ። ዓላማ ሳይኖረዉ የወጣ መኖሩ ያጠራጥራል። እግዚአብሔር ከሀገር እንድንወጣ የረዳን መሆኑን በአንድም በሌላም መንገድ ተናግረናል። ስለዚህ ይሕን ቃላችንን እናስታዉስና ለምን እንድወጣ ፈቀደልኝ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ስንወጣ የሎጥን ሚስት አስቧት የሚል ስንቅ አስቋጥሮን እንጂ እንዲሁ አይደለም። ወደ ኢትዮጵያ አትመልከቱ አይደለም፣ ወደ ቀደመ የሓጢአት ኑሮ አትመለሱ የምትሄዱበት ጽንፈ ዓለም ሓጢአት የነገሠበት ስለሆነ መጠራታችሁን አስታዉሱ የሚል ነዉ እንጂ። የሎጥ ሚስት ማንነቷን ረስታ፣ የመልአኩን ቃል ዘንግታ “ወይ አገሬ ሰዶም እግዚአብሔር ባላወቀ ፈርዶ አደረገሽ ባዶ” አለች፤ መጨረሻዋ ግን የጨው ሐዉልት መሆን ነው። ሰዉ ማንነቱን ከረሳ የጠላቶቹ (ሓጢአት፣ ሰይጣን) መፈንጫ እና መራገጫ መሆኑ አይቀርም። በዓላማችን ስንጸና ግን ያሰብነዉን ማሳካት እና ረጅም ጉዞ መጓዝ እንችላለን።
፭. በጸሎትና በአገልግሎት መትጋት፣ እርስ በራስም መተሳሰብ፦ ሰዉ ከእግዚአብሔር አምላኩ ጋር የሚገናኘው በጸሎት ነዉ። ጸሎት ሰዉን ከፈጣሪዉ ጋር የሚያገናኘው ረቂቅ ዓምደ ብርሃን በመሆኑ የክርስቲያኖች ሕይወት ከጸሎት ጋር ተለይቶ አይታሰብም። ከጠላት ፍላጻ ለመጠበቅ ጸሎት ፍቱን ነዉ። በአገልግሎት ያለ ሰዉ ስለ አገልግሎቱ፣ ስለ መንጋዉ መጨነቅ እና መጸለይ ይኖርበታል። ፈተናን በድል ለመወጣት አዘዉትረን መጸለይ ይገባናል። ቅዱስ ጳዉሎስ “የሰይጣንን ተንኮል መቋቋም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ። ሰልፋችሁ፦ ከጨለማ ግዦች ጋርና ከሰማይ በታች ካሉ ከክፉዎች አጋንንት ጋር ነዉ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ጋር አይደለምና። ስለዚህም በክፉ ቀን መቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ያዙ። እንድትጸኑም በሁሉ የተዘጋጃችሁ ... በጸሎትና በምልጃ ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፣” ኤፌ.፮፣፲፩- ፲፰ ሲል እንደመክረን።
በዚህ በባዕድ አገር ያለዉ ሁናቴ ኢትዮጵያ ዉስጥ ካለዉ የተለየ መሆኑ፤ ግለኝነት የተንሰራፋበት እና ለመንፈሳዊዉ ነገር ደንታቢስ የሆነዉ ሕዝብ ቁጥር መብዛት በመንፈሳዊ ሕይወት እንዳንጎለምስ፣ በጾም፣ በጸሎት እና በአገልግሎት ሌሎች ትሩፋቶችንም በማብዛት እንዳንተጋ ጫና ሊያሳድርብን ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን ከላይ ከፍ ብሎ የተመለከትናቸዉ ቁም ነገሮች ከፊት ይልቅ እንድንተጋ የሚያደርጉ፣ የጊዜዉን ሁናቴ እንድንመረምር እና ቃለ ወንጌልን እንድናስታዉስ የሚያስገድዱን ናቸዉ። ከሀገር መዉጣታችን ፍሬ እንድናፈራ መሆኑን ከተቀበልነዉ በጸሎትና በመንፈሳዊ አገልግሎት መትጋት ወደ መካከል መምጣትም ይገባናል። በምክረ ካህን የምንኖር፣ በንስሓ ሕይወት የምንመላለስ ከሆነንና ሕይወታችንን በቅዱስ ሥጋዉ እና በክቡር ደሙ ያተምን ከሆነ የሚገጥመንን ፈተና ሁሉ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ በአሸናፊነት ለመወጣት አያዳግትም፣ በእኛ የሚሠራ እርሱ አምላካችን ከአሸናፊዎች ሁሉ በላይ ነዉና። አኗኗራችን እንዲህ ከሆነ ለከተማዋ የታዘዘ ጥፋት ቢመጣ እንኳ እግዚአብሔር አምላካችን ከጥፋት ሊያድን የታመነ አምላክ መሆኑን ጻድቅ ሎጥና ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መላእክቱን በመላክ አሳይቶናል። ከአብርሃም እና ከሎጥ ጋር የነበረ እግዚአብሔር ዛሬም ያዉ ነው፣ ፍቅሩ በዘመን ብዛት የሚቀንስ የማዳን እጁንም የሚያጥፍ አይደለም። በድንቅ አጠራሩ የጠራን በቸርነቱ ጥላ ከልሎ እድሜ ለንስሓ የሰጠን፣ በፍቅሩ ከጥፋት እስከ አሁን የጠበቀን ቅዱስ እግዚአብሔር ቀሪ ሕይወታችንን እንዲያስተካክልልን፣ አገልግሎታችንን እንዲያሰፋልን፣ የመንግሥቱ ወራሾችም እንዲያደርገን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የእናትነት ፍቅርና ርኅራኄ፣ የቅዱሳን ጸሎት እና ምልጃ አይለየን፤ አሜን።
No comments:
Post a Comment