Monday, 23 May 2011

ተግባር የሌለው ምኞት /ክፍል ሁለት/


ምኞት የሚለው ቃል በግዕዙ ተምኔት ይለዋል ፈቃድ፣ ልመና ማለት ነው። ተመነየ ፦ ተመኘ፣ ፈለገ፣ ወደደ፣ ለመነ የሚል ትርጉም ይሰጠናል። "ተመነየ ይርአይ ዕለትየ ርእየሂ ወተፈሥሐ ። ቀኔን ያይ ዘንድ ተመኘ ሐሴት አደረገ" (ዮሐ 8፡56) "ወውስተ ብሔር እንተ ትትመነይ ነፍስክሙ ኢትገብኡ እንከ ህየ። ትመላለሱባት ዘንድ ነፍሳችሁ ወደምትመኛት ወደዚያች ምድር አትመለሱም" (ትን.ኤር 22፡27) እንዲል (ኪዳ.ክፍ ገጽ 299)።
በቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመዉረስ እንድንሻ ተነግሮናል "አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግስት ጽድቁንም ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል" (ማቴ 6፡33)። እናንተ ፈቃደ ሥጋችሁን ለፈቃደ ነፍስ አስገዝታችሁ፣ በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን ተጉዛችሁ፣ አስራት አውጥታችሁ፣ ሥገወደሙ ተቀብላችሁ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እሹ፣ ፈልጉ የዚህ ዓለም ነገር ምግባችሁን፣ ልብሳችሁን፣ ኑሮአችሁን ግን የሰማይ አባታችሁ እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና እርሱ እራሱ እንደ ዳረጐት ይጨምርላችኋል ሲለን ነው።
በሌላም በኩል እግዚአብሔር ምሕረት እንዲያደርግልን እንድንሻ በቅዳሴው ሥርዓት ላይ ተጽፎልናል። ገባሬ ሰናይ ዲያቆን በሚያዜመው የመጀመሪያው ጸልዩ የሚል አዋጅ ጸልዩ ካለን በኋላ የሚከተለውን ምክር ይመክረናል "ኅሡ ወአስተብቊዑ ከመ ይምሐረነ እግዚአብሔር ወይሣሃል ላዕሌነ። እግዚአብሔር ይምረን ዘንድ በኛም ላይ ይቅር ይል ዘንድ እሹ ለምኑ" (ሥርዓተ ቅዳሴ)። የእግዚአብሔርን ምሕረት መሻት መመኘት ለዚህም መጸለይ ንሰሐ መግባት ለክርስቲያኖች የሚገባ ነው።
ልበ አምላክ የተባለ ነብየ ልዑል ቅዱስ ዳዊትም እንዲህ ይላል "አሐተ ሰአልክዎ ለእግዚአብሔር ወኪያሃ አኀሥሥ ከመ እህድር ቤቶ ለእግዚአብሔር በኵሉ መዋዕለ ሕይወትየ" "እግዚአብሔር አንዲት ነገር ለመንሁት እርሷንም እሻለሁ በህይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ" (መዝ 26፡4)። በእግዚአብሔር ቤት መኖር ከሁሉ ይልቅ መልካም ነው። ሠላም፣ ፍቅር፣ በረከት ሁሉም አለበት። ይህንንም መለመን መሻት የዚህ ሁሉ ባለቤት ያደርጋል።
መንፈሳዊን ነገር መሻት፣ መመኘት መልካም ሆኖ ብቻዉን ግን ዋጋ አይኖረዉም። ምኞት ከተግባር ጋር መጣመር አለበት። የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ፣ ምሕረት ለማግኘት፣ በቤተ መቅደስ ለመኖር ከእኛ የሚጠበቅ ነገር አለ። መጦም፣ መጸለይ፣ ንሰሐ መግባት፣ መቁረብ፣ አሥራት ማውጣት የእኛ ድርሻ ነዉ። ከዚህ ውጭ ሆነን ያለምንም ሥራ በመመኘት ብቻ ግን መንፈሳዋዊዉን በረከት ማግኘት ብንሻ ግን አይሆንልንም፣ አይሳካልንም። በባዶ ሜዳ ብዙ እየተመኙ ውሎ ከማደር የፈጣሪን እርዳታ እየጠየቁ በትንሹም ስራ መጀመር ተገቢ ነው።
ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ "ሰው የተመኘውን ከሠራ የሚጠብቀው ሞቱን ነው" ብለዋል። ብፁዕነታቸው ዝዋይ በረሃ ላይ ወድቀው የሚገባቸዉን ሠርተዉ ምኞታቸዉን እዉን አደረጉ እንጂ ያለምንም ሥራ መና ከሰማይ ይዉረድልኝ አላሉም፡፡ በየክፍለ ዓለማቱ ወጥተው ወርደው ምኞታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ባይደክሙ ዛሬ የምናየውን ፍሬአቸውን ባላየንም ነበር።
መንፈሳዊውን ነገር መመኘት መሻት ከላይ እንዳየነው ይሆንና ወደ ሥጋዊ ኑሮአችን ስንመለስ ግን ከዚህ ለየት ይላል፡፡ በሥጋዊው ኑሮአችን ለምንመገበዉ፣ ለምንለብሰው እንድንጸልይ ተነግሮናል "የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ" እያልንም እንጸልያለን። በምስጢር የተቀመጠው የነፍሳችን መድኃኒት የጌታችንን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ሲሆን በሰሙ ግን የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ስጠኝ ነው። ይህንን መለመን ኃጢአት አይደለም፡፡ ቤተሰባችንን የምንመራበት ልጆቻችንን የምናሳድግበት የዕለት ጉርስ ያስፈልገናል። ከዚህ ባለፈ ግን ብልጥግናን እንድንመኝ፣ እንድንሻ፣ እንድንለምን አልተነገረንም።
ጠቢቡ ሰሎሞን "ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ እንዳልጠግብ እንዳልከዳህም እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል ድሃም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል" (ምሳ 30፡8) ይላል። ብልጥግና ከሠራን ከወጣን ከወረድን በራሱ ጊዜ ሊመጣ ይችላል። ላይመጣም ይችላል። እኛ ግን የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ከመጠየቅ በላይ ስለብልጥግና እንድንጨነቅ አልተፈቀደልንም።
ወደ መንግሥተ ሰማያት በምናደርገው ጉዞ ብልጥግና ለነፍሳችን የሚጠቅም ከሆነ እርሱ በራሱ ጊዜ ያደርገዋል። ከዚያ ውጪ የዕለት ጉርስ ሰጥቶ በመንፈሳዊ ተግባር እንድንጠመድ ሊያደርገንም ይችላል። ሁሉም አላፊ ስለሆኑ በአኩቴት እንቀበላቸዋለን። ሌሊት ተነስቶ ሎተሪ ቢደርሰኝ ጠዋት በማለዳ ባለጠጋ ብታደርገኝ እያልን መጨነቅ ግን ጉዞአችንን እንድንረሳ ያደርገናል። የመንግሥተ ሰማያት ነገር እየተዘነጋ በምድራዊ ምኞት ሰጥመንም እንቀራለን። "ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ምትረፊያ ነው ወደ ዓለም ምንም እንኳ አለመጣንም እና አንዳችም ልንወስድ አይቻለንም ምግብና ልብስ ከኖረን ግን እርሱ ይበቃናል። ዳሩ ግን ባለጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በመጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የጥፋት ሁሉ ስር ነው አንዳንዶች ይህን ሲመኙ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ስቃይ ራሳቸውን ወጉ።" (2ጢሞ 6፡6) በማለት ቅዱስ ጳዉሎስ የሚመክረንም ለዚህ ነዉ።
ብልጥግና ለአንድ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ለሚያምን የሚሰጠው የአምላክ ፈቃድ ሲሆን ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ በመመኘት ብዛት አይሆንም። አምላክም ደግሞ ይህን የሚያደርገው ይህ ክርስቲያን በተሰጠው ሀብት የሚጠቀም ከሆነ ነው፣ የሚሰናከል፣ የሚጠፋበት ከሆነ አይሰጠዉም። ጠቢቡ ሰሎሞን እንዳለ "እግዚአብሔር ማን ነው?" የሚልበት ከሆነ አይሰጠውም። ለመንፈሳዊ ሰው ደግሞ የዕለት ጉርስ ካገኘ መበልጠግም ሆነ አለመበልጠግ ልዩነት የላቸውም። ልቡናዉ ሰማያዊ ስለሆነ ኑሮዬ ይበቃኛል እያለ ይኖራል።
በዘመናችን አንዳንድ ሰው ካልበለጠኩኝ ምኑን አምላኬ ሆንከው የሚል አለ። ቤትህን እሰራለሁ በሚል ሰበብ ሎተሪ ካልደረሰኝ ምኑን ፈራጅ ሆንከው የሚልም አይጠፋም። ይህ ፈቃደ እግዚአብሔርን ያለማወቅ ነው።ከዚህ ይልቅ "ወይኩን ፈቃድከ" "ፈቃድህ ይሁን" ብለን ህይወታችን በእርሱ ፈቃድ እንዲመራ ብናደርገው ነፍሳችንን እናሳርፋታለን።
እውነታው ይህ ሆኖ ጊዜያዊውን ከዘለዓለማዊው መለየት ለምን ተሳነን? በብልጥግና ምኞት ብቻ ጊዜያችንን እንድናባክን ለምን ሆነ? እናቱ እንደሞተበት ልጅ ባለመበልጠጋችን እንድናዝን እራሳችንን እንድንጠላ ለምን ሆነ? ያለን ይበቃናል ተመስገን ማለት እንዳንችል የብልጥግና ምኞት ለምን ሰለጠነብን?

No comments:

Post a Comment