Monday, 23 May 2011

ተግባር የሌለው ምኞት /ክፍል አንድ


ሰው መኖር ያለበት የተሰጠውን የሚችለውን ብቻ ነው። የተሰጠዉን ትቶ በቅዥት ዓለም መኖር ከጀመረ በምኞት ፆር ተወግቷል ማለት ነው። ምኞት ደግሞ ጸንሳ ኃጢአትን ኃጢአትም ሞትን ስለሚወልዱ / ያዕቆብ 1-15/ በምኞት የተወጋ ሰዉ ለሞት ሊዳረግ ይችላል።አንድ የማውቀው ሰው ነበር፤ ሀገር ቤት እያለሁ ሁል ጊዜ ስንገናኝ አዲስ አዲስ ሀሳብ ይዞ ይመጣል። እንዱንም ግን አይፈፅመውም አይደለም መፈጸም አይጀምረዉም።ብቻ ሁል ጊዜ ያልመዋል። አንድ ቀን የእርዳታ ድርጅት መስርቶ /በሃሳብ ነዉ/ ይመጣል ሌላ ጊዜ የአ/አ ክልል ስራ የፈቱ ወጣቶች የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል ከፍቶ ይነግረናል። ይህም በሃሳብ ነው። ሲለው ደግሞ መርካቶ አካባቢ የንግድ ባለሙያዎችን ማማከሪያ ጽ/ቤት ይከፍትና ነጋዴው የሰለጠነ አሰራር እንዲኖረዉ ለማድረግ አቅዶ ይመጣል። ብቻ ሕልሙ ምኞቱ ማለቂያ የለውም፤ ሁልጊዜ ኣዲስ ነው። ታዲያ ከታሰቡት ሀሳቦች የተጀመረ አንድም አላስታውስም። ሁሉም በወረቀት ላይ ማስታወሻ ከመሆን አያልፍም።
ወደ ሰሜን አሜሪካ ስመጣ ህዝቡ በሠለጠነ ሀገር ስለሚኖር እንዲህ ዓይነት ልማድ በአንድ ፐርሰንትም አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ግን ብሶበት አረፈው። አንዳንድ ሰሜን አሜሪካ ያሉ አትዮጵያዊያን ትልቁ ችግር የተሰጣቸውን ኑሮ ከመኖር ይልቅ የማይኖረውን ኑሮ እያለሙ መመኘት እንደሆነ ተረዳሁ። ሎተሪ ሲደርሳቸው ባጋጣሚ የተፈጠረ ዕድል ሲቀናቸው፣ ሳይታሰብ የመጣ ብልፅግና ደርሶ ሲጎበኛቸዉ እያሰቡ ብልፅግናን የሚመኙ ከሥራ ይልቅ ምኞትን የሙሉ ጊዜ ሥራ ያደረጉ ጥቂት አይደሉም።
ትምህርት እየተማርክ ነው? ለመማር አስቤያለሁ ከጀመርኩ ግን በደንብ መሆን አለበት። ማስተርስ ወይም ፒ.ኤች.ዲ ካልሆነ በትንሹ አልሞክረውም የሚሉ መልሶች ሰሜን አሜሪካ ላይ የተለመዱ ናቸው። ኮሚዩኒቲ ኮሌጅ ገብቶ የመጀመሪያውን ደረጃ ለማለፍ ዳገት ሆኖባቸው ፒ.ኤች.ዲ ካልሆነ የሚሉ ኢትዮጵያውያን ሳይጀምሩ ያጠናቀቁ፣ ሳይወጥኑ የፈጸሙ ናቸው። አንዱንም ሳይዙ በአሶሺየት ዲግሪ በተመረቁ ወገኖች የሚቀልዱ ፤ ስለተመኙ ብቻ የተመረቁ እየመሰላቸው በተለያየ ሙያ አስተያየት መስጠት የሚያበዙ ጥቂቶች አይደሉም።
ቤት ገዝተሃል? አይ ቤት አልገዛሁም እኔ ከገዛሁ ቢች አካባቢ ነው የምፈልገው እንዲያውም የእኔን ቤት ሰሞኑን ወስጄ አሳይሃለው የሚሉም አጋጥመውኛል። ትልቅ ቤት ተፈልጎ በሚሊዮኖች የሚያወጣ ቪላ አሳይተው ይሄ ነው የኔ ቤት ሎተሪ ከደረሰኝ እዚህ ነው የምገባው የሚሉ አሉ። አሁን ካሉበት ሕይወት ለመሻሻል ግን ምንም ዓይነት ጥረት አያደርጉም በሚችሉት በአቅማቸው ቢያንስ አነስተኛ ቤት ለመግዛት አንድ እርምጃም አይራመዱም ።
ንስሐ ገብተሃል ቆርበሃል? አይ ገና ነኝ ብዙ የማስተካክለው ነገር አለ። በዛ ላይ ኢየሩሳሌም ሄጄ መቁረብ ነው የማስበው የሚሉ ለመቁረብ አንድ እርምጃ ሳይራመዱ በምኞት ብቻ ጉዳዮችን እንዳይፈቱ አድርገው የሚያወሳስቡም አይጠፉም። አንድ ስቴት ያገኘኋቸው ባልና ሚስት ቆርባችኋል? አልኳቸው፤ አሄሄ አሉ ገና ነን ከቆረብን ግሸን ማርያም ሄደን በሬ አርደን ድግስ ደግሰን ነው። በዚያ ላይ ከመቁረባችን በፊት ቤት መስራት እናስባለን ከዚያ ለእንግዳ ማረፊያ አንድ ክፍል እንሰራለን፤ የገዳም አባቶች ሲመጡ እዚያ እያረፉ ይፀልዩልናል ሌላም ሌላ አሉ። በዝምታ ካደመጥኩ በኋላ ሃሳባቸው ጥሩ እንደሆነ ነገር ግን ሞት ቀጠሮ ስለሌለው በእጃቸው ያለውን ጊዜ ያለምንም ውጣ ውረድ እንዲጠቀሙበት መከርኳቸው ፤ እነዚህ ሰዎች አሜሪካን ለቀው ኢትዮጵያ የሚገቡት መች እንደሆነ እግዚአብሔር ይወቀው። በዚያ ላይ ደግሞ ቤት እስኪሰራ ድግስ እስኪደገስ የቁርባኑ ነገር ዕቅድ ሆኖ ቀረ ማለት ነው። በምኞት ብቻ መኖር ይሄ ነው።
የቤተክርስቲያን የአባልነት ክፍያ ከፍለሃል ሲባሉም 20 እና 30 ዶላር መክፈል መፍትሄው ሆኖ ሳለ እስኪ እኔ አንደኛዉን አስራት መጀመር አስባለሁ የሚሉ ግን የማይጀምሩ። መልካም ።አስራት ለምን አታመጡም ሲባሉ እኔ ለዚህ ቤተክርስቲያን የማስበው ሌላ ሃሳብ አለኝ። እስኪ ፀልዩልኝ። አንድ የምጠብቃት ነገር አለች እርሷ ከተሳካች ሞርጌጁን እዘጋለሁ ወይም ከባድ ነገር አደርጋለሁ እያሉ ብቻ የሚኖሩም አሉ። ለትልቁ ስራቸው ጅማሬው የአባልነት መዋጮ በትክክል መክፈል መሆኑን አልተረዱትም በትንሹ ሳይታመኑስ በትልቁ እንዴት ሊታመኑ ይችላሉ።
ከላይ ባሉትና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ በስራ በተግባር ከመጀመር ይልቅ በምኞት ብቻ የሚኖሩትን ሳይ አሜሪካ የምኞት ሀገር ነው አልኩኝ። በእርግጥ መመኘት አይከፋም ግን ምኞትን ሥራዬ ብሎ መኖር እንዲሁም ሳይጀምሩ በባዶ ሜዳ ይሄን እሆናለሁ ይሄኛው ይሻለኛል ብሎ ማለትም በራሱ የቀን ሕልመኛ ያደርጋል እንጂ ለሕይወት መፍትሄ አይሆንም። አብዝቶ ከመመኘት ጥቂትም ቢሆን የቻሉትን መስራት፤ ኑሮን ዛሬ መጀመር ተገቢ ይመስለኛል።
ለዛሬ በዚህ ይቆየንና በሚቀጥለው ጽሑፍ ክርስቲያኖች ለክፉ፣ ተግባር ለሌለዉ ምኞት የሚጋለጡባቸውን በሃሳብ ብቻ እንዲኖሩ የሚያደርጓቸውን ምክንያቶች በመጠኑ እንመለከታለን። ለሁሉም እግዚአብሔር ይርዳን።

No comments:

Post a Comment